Genesis 29

ያዕቆብ መስጴጦምያ ደረሰ

1ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ። 2እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጕድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጕድጓድ ሲሆን፣ የጕድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው። 3መንጎቹ ሁሉ በጕድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጕድጓዱን አፍ ይገጥሙታል።

4ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።

እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት።

5እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው።

እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት።

6ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው።

እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ነች” አሉት።

7ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው።

8እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጕድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በስተቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ።

9ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። 10ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጕድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ። 11ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 12ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው።

13ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። 14ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ነህ” አለው።

ያዕቆብ ልያንና ራሔልን አገባ

ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ አብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣
15ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው።

16ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። 17ልያ ዐይነ ልም
ወይም አደጋ የማይችል ዐይን
ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር።
18ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው።

19ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ አብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወድዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው።

21ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቷል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው።

22ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። 23ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም አብሯት ተኛ። 24ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጡር እንድትሆን ሰጣት።

25ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጕድ ሠራኸኝ? ያገለገልሁህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው።

26ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ 27ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።”

28ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋር ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፣ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤ 29ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጡር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት። 30ያዕቆብ ከራሔልም ጋር ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው።

31 እግዚአብሔር (ያህዌ) ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። 32ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወድደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል
ሮቤል የሚለው ቃል ሥቃዬን ተመልክቶ የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተመሳሳይ ድምፅ አለው፤ የስሙ ትርጕም ግን ማየት፣ ልጅ ማለት ነው።
አለችው።

33እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን
ስምዖን ማለት የሚሰማ ማለት ሊሆን ይችላል።
ብላ ጠራችው።

34አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ
ሌዊ የሚለው ቃል የተያያዘ የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን ከዚሁ ቃል ጋር አንድ ዐይነት ድምፅ አለው።
ብላ ጠራችው።

35እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ
ይሁዳ የሚለው ቃል ውዳሴ የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር አንድ ዐይነት ድምፅ አለው።
ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች።

Copyright information for AmhNASV